Back

አዲሱ የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር በአገራችን የፌዴራል ሥርዓታችን ጤናማና ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተገለፀ ፤

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዲሱን የጋራ ገቢዎች ቀመር አስተዳደርና አተገባበር ለመገምገምና የመረጃ አያያዝ፣አቀራረብና አጠቃቀምን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የተከበሩ አቶ አደም ፋራህ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ ሲሆኑ የፌዴራል መንግስትና የክልሎች የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈልበት ቀመር ከ23 ዓመት በኋላ ተሻሽሎ ከሐምሌ 1/2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑን ተናግረው ይህም የክልሎችን የጋራ ገቢዎች ድርሻ በከፍተኛ ደረጃ ከማሳደጉም በላይ የፌዴራል ሥርዓታችን ጤናማና ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ገልፀዋል፡፡
ምክር ቤቱ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 62 መሰረት በፌዴራል እና በክልሎች መካከል የጋራ ገቢዎች የሚከፋፈልበትን ቀመር ለመወሰንም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን የድጎማ በጀት የሚከፋፈልበትን ቀመር በጥራትና በፍትሐዊነት ለመወሰን የተሟላና ጥራታቸው የተጠበቀ መረጃዎች እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ የሚመለከታቸው የመረጃ አመንጪ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ወቅታዊ፣ ታዓማኒና ትክክለኛ መረጃዎችን በአግባቡ መያዝና በሚጠየቁበት ጊዜ ማቅረብ እንዳለባቸው ተግልጿል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ምክር ቤቱ ውጤታማ የፊሲካል ሽግግርና ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል ለማረጋገጥ የሪፎርም ሥራ የጀመረ መሆኑን አፈጉባኤው ገልጻው ለውጤታማነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳላ ማህበራዊ ፍትህን በሚያረጋግጥ መልኩ በክልሎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገት እንዲመዘገብ ለማድረግ የክልል መንግሥታት ከሁሉም የበጀት ምንጮች የሚሰበስቡትንና የሚያገኙትን ገቢ ለተገቢው ዓላማ ግልፅነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ለሕዝብ ጥቅም ሊያውሉት ይገባል ያሉት አፈጉባዔው ከሃዲዎቹ የቀድሞ የትግራይ ክልል አመራሮች ከተሰጣቸው ሕገ መንግስታዊ ሥልጣን ውጭ በጀቱን አፋራሽ ለሆኑ ተልዕኮዎች ያዋሉ በመሆናቸው በሕግ ሊጠየቁ ይገባልም ብለዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የጋራ ገቢዎችና የድጎማ በጀትን ወይም የሃብት ክፍፍልን ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ የተሻሻለውን የፌዴራል መንግስትና የክልሎች የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን በማድነቅ በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የመንግስት ሠራተኞች ስታትስቲካል መረጃዎች እንዲሁም የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ መረጃዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቁመው በአጠቃላይ ከዚህ ዓላማ ጋር ተያይዞ ያሉ ማንኛውም መረጃዎች ግልፅነት፣ታዓማኒነትና ወቅታዊነት እንዲኖራቸው ሁሉም በባለቤትነት ስሜት የበኩላችንን እንድንወጣ በማለት ያሳሰቡ ሲሆን ይህም በፌዴራል ሥርዓታችንና በአብሮነታች መተማመን፣ የተጠናከረ አንድነትና ግልፅነት ከመፍጠሩም በላይ ለዘላቂ ሠላማችን አንዱ መሠረት ይሆናል ብለዋል፡፡
በውይይቱ ከሁሉም ክልሎች ገቢዎች ቢሮ፣ ገንዘብና ኤኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ፕላንና ልማት ኮሚሽን እንዲሁም ከፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ከፌዴራል ፕላንና እቅድ ኮሚሽን፣ ከማዕድንና ፔትሮሊየም ሚኒስቴርና እና ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች ተሳትፈውበታል፡፡
ህዳር/2013 ዓ.ም