የአፈ-ጉባኤመልዕክት
የአፈ-ጉባኤ መልዕክት
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፌዴራሉ መንግሥት አባል ክልሎች የሚገኙት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የሚልኩዋቸው አባላት የሚወከሉበት ምክር ቤት ነው፡፡ ምክርቤቱ የሕገመንግሥት የበላይነት ሰፍኖ፣ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች በሁሉም መስክ እኩልነታቸውና የፈጣን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ተረጋግጦ፣ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ፣ ሥር የሰደደ አንድነት እና ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዳብሮ የማየት፣ ራዕይ ሰንቆና ሕገመንግሥቱን በመተርጎም፣ በመፈቃቀድ እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ የሕዝቦች አንድነት ሥር እንዲሰድ እና እንዲዳብር በማድረግ፣ በክልሎች መካከል ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ግንኙነቶችን በማዳበር፣ ፍትሀዊ እና ውጤታማ የድጎማ በጀት እና የጋራገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር በማዘጋጀት እና በመወሰን፣ ሕግ ሊወጣላቸው የሚገቡ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን በማጥናት እና በመለየት፣ እንዲሁም ዜጎች ሕገመንግሥቱን ጠንቅቀው አውቀው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት በቁርጠኝነት የመሥራት ተልዕኮ አንግቦ በሕገመንግሥቱ ተለይተው የተሰጡትን ሥልጣን እና ተግባር ለመወጣትና ውጤታማ ለመሆን እየተጋ ይገኛል፡፡
የሕገመንግሥቱን የበላይነት ከማረጋገጥ አኳያ ሕገመንግሥቱን በመተርጎም፣ የሃብት ክፍፍሉ ፍትሓዊነት እንዲረጋገጥ የማከፋፈያ ቀመር ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍትሀዊ እና በሁሉም ተቀባይነት ያለው ቀመር ያዘጋጃል፡፡ ተደብቀው የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በሕገመንግሥቱ እውቅና አግኝተው ማንነታቸው ተረጋግጧል፤ የቋንቋዎች ፤ የባህል እና የሀይማኖት እኩልነት በሀገሪቱ እንዲረጋገጥ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እኩልነታቸውና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብሮላቸው ራስን በራስ ከማስተዳደርም በላይ በአገራዊ ጉዳዮች እኩል ተሳታፊ እና የወሳኝነት ሚና እንዲጫወቱ ምክር ቤቱ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡
ብዝኃነትን በዴሞክራሲያዊ አግባብ በማስተናገድ በመቻቻል እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አገራዊ አንድነት ሥር እንዲሰድ ምክር ቤቱ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ምክር ቤቱ አሰራሩን ከማሻሻል አኳያ ከአገራዊ እና አለማቀፋዊ ሁኔታዎች ለውጥ አንጻር ውስንነቶቹን እየፈተሸ ጠንካራ ተሞክሮዎችን በይበልጥ እያሸጋገረ እና የአገሮችን ስኬታማ ልምዶችን እየቀመረ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በተሸለ ሁኔታ በሚያረጋግጥ መልኩ ቀጣይ አሰራሮችን በአዲስ ለውጥ መንፈስ ለመሥራት በቁርጠኝነት ተዘጋጅቷል፡፡ ለተግባራዊነቱም ለምክር ቤቱ ድጋፍ የሚሰጠው ጽ/ቤቱን የእስካሁኖቹን መዋቅራዊ አደረጃጀት እና የአሰራርና የአፈጻጸም ሁኔታዎችን በመፈተሸና በመገምገም ላይ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ ይህንን ዓላማ በጽ/ቤቱ ውስን ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ብቻውን ማሳካት ስለማይችል፤ የክልል መንግሥታት፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፣ እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት የጎላ ተሳትፎ እንዳይለየው መልዕክቴን እስተላልፋለሁ፡፡
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ